ከኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን የኢንቨስትመንት ባንክ ፈቃድ የተሰጠው ወጋገን ካፒታል ኢንቨስትመንት ባንክ በይፋ አገልግሎት መጀመሩን አብስሯል።
ይኽ ኢንቨስትመንት ባንክ ሙሉ ለሙሉ ከወጋገን ባንክ የተለየ እና ራሱን የቻለ ተቋም መሆኑን የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ የሆኑት አክሊሉ ውበት (ዶ/ር) በዕለቱ ገልጸዋል።
ቲክቫህ ኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ባንኩን ወደ ገቢያ ለማስገባት ምን ተግዳሮት ነበረው ? ሲል ዋና ሥራ አስፈጻሚ የሆኑትን ብሩክታዊት ዳዊትን ጠይቋል።
ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ " አዲስ ማርኬት እንደመሆኑ መጠን በዚህ የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማግኘት በጣም አስቸጋሪ ነበር። በዚህ ምክንያት ከውጭ ማምጣት ነበረብን በዚህም ሁለት ኤክስፐርት በስልጠና እና በማማከር ተቀጥረዋል " ሲሉ ገልጸዋል።
ሁለቱ ሰራተኞች ስራ እንዲሰሩ ብቻ ሳይሆን ሰራተኞቹን እንዲያሰለጥኑ ጭምር መቀጠራቸውን፤ ይሄም በጣም ወሳኝ መሆኑንና ብቁ ሰራተኛ ያስፈልግ እንደነበር ተናግረዋል።
- የኑሮ ውድነት ( Inflation )፤
- የውጭ ቀጥታ ኢንስትመንት ብዙ አለመኖር፤
- የምንዛሬ ተመኑ መዋዠቅ
- የተረጋጋ ማክሮ ኢኮኖሚው አለመፍጠሩና ሌሎችም ፈተናዎች እንደነበሩ ጠቅሰው እሱን አልፈው ለዚህ መድረሳቸውን አስረድተዋል።
ኢንቨስትመንት ባንኩ፥ የድርጅቶች የሽያጭ እና መዋኻድ ሂደት፤ ዳግም ማደራጀት ውጤታማ እንዲሆኑ ማገዝ፤ የድርጅት ድርሻ መሸጥ ወይም የብድር ሰነድ በመሸጥ ካፒታል እንዲያሰባስቡ ማገዝ ያሉ ሥራዎችን ይሰራል።
በተጨማሪም፥ ድርጅቶች ለመጀመሪያ ጊዜ በሰነደ መዋዕል መገበያያ ላይ ቀርበው ድርሻቸውን እንዲሸጡ፤ የብድር ሰነድ እና ሼር ንግድ በግለሰቦች እና በኢንቨስተሮች መካከል የተቀላጠፈ እንዲሆን እና ካፒታል የሚፈልጉ ድርጅቶችን ካፒታል ካላቸው ኢንቨስተሮች ጋር ማገናኘት ያሉ ሥራዎችን እንደሚሰራ ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ጠቅሰዋል።
በዕለቱ የተገኙት የኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገቢያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር ጥላሁን እስማኤል ለብዙዎች ውስብስብ የሆነውን ገቢያ ኢንቨስትመንት ባንኩ ለኢትዮጵያዊያን የገባ እና የቀለለ እንዲሆን ባንኩ እንዲሰራ ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ወጋገን ካፒታል ኢንቨስትመንት ባንክ ወደ ሥራ መግባቱን አብስሯል።
